የህዝባችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት ኅብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ተገለፀ።
(ህዳር 10/2017 ባሕርዳር) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ኅብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት “የኀብረት ስራ ሪፎርም ከማደራጀት ባሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ የኀብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ንቅናቄ መድረክ ያካሄደ ሲሆን በዚህም የከተማዋ ም/ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ፣የአብክመ የኀብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ አመራሮች ፣የልዩ ልዩ የኀብረት ስራ ማህበራት አመራሮች ፣አጋርና ባለድርሻዎች መገኘታቸው ተገልጿል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ኅብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ወርቁ በንቅናቄ መድረኩ መክፈቻ እንደገለፁት ኅብረት ስራ ማህበራት አሳሳቢ የሆኑ የህዝብን ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በውጤታማነት እንዲፈፀሙ እና ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ የመስራት ባህል የሚያዳብሩ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ተደርጎ በርካታና ውስብስብ የማህበረሰብ የመልማት ፍላጎቶችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለሆነም በኅብረት ስራ ማህበራት አሰራር የለውጥ ሪፎርም ማከናወን ለልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን እንዲሁም ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሚናው የጎላ በመሆኑ ካሁን በፊት ያልተፈቱና ለወደፊትም ለሚከሰቱ የጋራ ችግሮችን በተለይም የንግድና መሰል የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጥያቄዎችን ፣የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉ የምግብና ምግብ ነክ ፣የቁሳቁስ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት በኩል የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ ለመፍታት ዘመኑን የዋጅ ሪፎርም በየጊዜው ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል።
የአብክመ የኀብረት ስራ ማህበራት ባለስልጣን ም/ኃላፊ ወ/ሮ የዝና ደስታ በመክፈቻ መድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት ለኅብረት ስራ ማህበራት መጠናከርና ለህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ተደራሽነትና ውጤታማነት መሳካት በየጊዜው የሚሻሻሉ ሪፎርሞችን በመጠቀም ለሁለንተናዊ እድገታችን ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በማመን በባህርዳር ከተማ ይህ የንቅናቄ መድረክ መካሄዱ የሚመሰገን ተግባር ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኀብረት ስራ ማህበራት በርካታ መሆናቸውንና ከ247 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጀት አቅም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ በተለይም በእንስሳት ተዋፅኦ ፣በምግብ እህል አቅርቦት ፣በአትክልትና ፍራፍሬ ፣በሸቀጣሸቀጥ እና ሌሎች የምግብና ቁሳቁስ አቅርቦት ተግባራትን ተደራሽ በማድረግ በኩል እየተደረገ ባለው ጥረት በርካታ ስኬቶች እንደተገኙ ሁሉ ያልተፈቱ ችግሮችም በዚያው ልክ እየሰፉ በመምጣት አሁን እያየነው ላለው የኑሮ ውድነት እየዳረጉን ስለሆነ ሁሉም አካል ለጋራ ችግር በጋራ የመቆም ልምድን ሊያዳብር እንደሚገባ ገልፀዋል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፈ አቶ ጊዜው ታከለ በበኩላቸው የኅብረት ስራ ማህበራት ዘመኑን ሊመጥን የሚችል አገልግሎት እንዲሰጡ በበጀት ፣በአደረጃጀትና መዋቅር ፣በግብኣት ፣በአሰራር እና መሰል ጉዳዮች በመደገፍና በማጠናከር በአሁኑ ጊዜ ስር እየሰደደ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማሻሻል ፣የመኖሪያ ቤትን እጥረት ለመፍታትና ሌሎች የማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎቶችን ለማሳካት ትልቁን ሚና እንዲወጣ በማድረግ ረገድ መንግስት ከፍተኛ ሚና እየተወጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ዘላቂና ተደራሽነት ያለው ውጤት በማስመዝገብ በኩል አሁንም ገና የሚቀሩን ዘርፈ ብዙ የሆኑ የጋራ ጥረቶች በመኖራቸው የኅብረት ስራ ማህበራትን በየጊዜው በማነቃቃት የህዝባችንን አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በመድረኩ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት ለህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር መሻሻልና ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስፈን በአንድ በኩል የኅብረት ስራ ማህበራት በነበራቸው የአፈፃፀም ሂደት የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ግድፈቶችን በማረም እንዲሁም የበጀት ፣የአፈፃፀምና መሰል የአቅም ውስንነቶችን በማጠናከር በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ አዳዲስ የኅብረት ስራ ማህበራትን በማስፋት የእድገት ማነቆ እየሆነብን የመጣውን የኑሮ ውድነት ተግዳሮት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።





All reactions:
1717
