”ተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ሃብት መፍጠር የቻሉ የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ኀብረት ስራ ማህበራት እየተፈጠሩ ነው” ወ/ሮ የዝና ደስታ

ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (ኀ/ስ/ማ/ማ/ባ)

የአብክመ ኀብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን በማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማህበራት የተሰሩ ስራዎች እቅድ አፈፃፀም በምዕራብ አማራ ከሚገኙ የዞንና የከተማ አስተዳደር የኀብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ተ/ጽ/ቤትና ከግብርና መምሪያ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የዚህ ፎካል ፐርሰን በተገኙበት ገምግሟል፡፡

በዘርፋ የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማህበራት በአካባቢያቸው ላይ የሚታይ ውጤት ማምጣት መቻላቸውን ጠቁመው በዘርፋ የተመዘገበው ውጤት በዘላቂነት ለማስቀጠል ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ቅንጅተዊ ስራዎች ወሳኝ እንደሆነ የአብክመ ኀብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ም/ኃላፊ ወ/ሮ የዝና ደስታ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ከማህበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች አንዱ የሆነው የተፋሰስ ስራ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እና በግብርና ምርት ስርዓቶች ላይ ለሚተገበሩ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሂደቶች ውጤታማነት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ኀብረት ስራ ማህበራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር ለአባላት የገቢ ምንጭ ሁኗቸው ሃብት እንዲፈጥሩ ያስቻለ በመሆኑ የተፋሰስ ልማትን ባለቤት ሁኖ መስራት፣ተገቢውን የድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን በ2017 አፈፃፀሞች ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና የነበሩትን ክፍተቶች በሚሞላ የ2018 በጀትን በተገቢው መስራት እንደሚገባ ለዚህ ተቀናጅቶ በመስራት ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በእለቱ የማህበረሰብ የተፋሰስ ልማት ኅብረት ሥራ ማህበራት የስራ እንቅስቃሴ ሁሉም ዞን እና ከተማ አስተዳደሮች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መዳረሻ ግቡ ተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ የሚቆም ሳይሆን ለግብርና ልማት መሰረት መጣል ሲሆን የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማት አማራጮች በማስፋትና በማሳደግ ኑሮውን ማሻሻል ነው።

በአማራ ክልል የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ኀብረት ስራ ማህበራት በክልሉ 3891 ሲሆኑ የአባላት ቁጥር ከ640 ሺህ በላይ በመያዝ እና ካፒታላቸው 670 ሚሊየን 817 ሺህ 263 ይዘው በገቢ ማስገኛ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በለሙ ተፋሰሶች ወጣቶችን በማደራጀት በፍራፍሬ ልማት፣ በማድለብ፣ በንብ ማነብ እና መሰል ስራዎች የስራ እድል ፈጥሯል። ተፋሰሶችን በተሻለ መንገድ የሀብት ምንጭ ለማድረግ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር እጅግ ወሳኝ እንደሆነም ተገልፃል፡፡

የተፋሰስ ስራዎች ዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው ህብረተሰቡ ከተፈሰሶች ተጠቃሚ ሲሆኑ እና የባለቤትነት ስሜት የሚፈጠረውና ዘላቂነት የሚረጋገጠው አሰራርና አደረጃጀት ዘርግቶ ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በተጨማሪ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት የባለድርሻ አካላት የጋራ እርብርብ የሚጠይቅ፣ በተፋሰስ ልማት ዘርፈ ብዙ ተግባራት የሚከናወንበት በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ሁሉ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል።

የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት የተናጠል ሳይሆን የትብብር ስራ ነው። ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በተናጠል ውጤት ከማምጣት ይልቅ በትብብር ውጤት ማምጣት ተያይዞ ለማደግ፣ ለመለወጥ እና የጋራ ግብን ለማሳካት የሚያስችል ነው።

አባላት ከልቅ ግጦሽ የተጠበቁ የወል መሬዎች ላይ መኖ በማልማት፣ ከብቶችን የማድለብ ፣የደሮ እርባታ ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማትም የገበያ ሰብሎችን ማልማትና አመጋገባቸውን ማሻሻል የቻሉ ሲሆን ለወጣቶች፣ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኛ ማህብረሰብ የስራ ዕድል በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተፋሰሱ ለተደራጁት ተዘዋዋሪ ብድር 832 ሚሊየን 922 ሺህ 038 ብር አግተዋል፡፡

በመጨረሻም በተፋሰስ ልማት ኀብረት ስራ ማህበራት የተደራጁትን ዘላቂነታቸው አና ውጤታማነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው የሂሳብ አያያዛቸውን የማዘመን፣አመራሩን የማጠናከር፣ህጋዊ አሰራርን የማስፈን እና ለስራው አመራሩና ባለሙያው ባለቤት በመሆን ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ተገልፃል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top