ግንቦት 15/2018 ዓ.ም( ኀ/ስራ ኮሚሽን) በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው የመኖሪያ ቤት ቦታ መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን የቁጠባ ባህልን ለማሳደግና የቤት ባለቤት መሆን መስራት እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ለተደራጁ ማህበራት የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከተማ አሰተዳደሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በአማራ ክልል ያለውን የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሞላ መልካሙ ገልፀዋል።
መንግስት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ የገባውን ቃል እየመለሰ መሆኑን የማህበራቱ የመኖሪያ ቦታ ርክክብ ማሳያ መሆኑን ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
መንግስት የተለያዩ የመኖሪያ ቤት አማራጭ ፓሊሲዎችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ቢሮ ኃፊው መሬትን በምደባ ማስተላለፍ በስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት አማረ ደግሞ መንግስት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት 6 ወራት 59 ማህበራት የመኖሪያ ቤት ቦታ መውሰዳቸውን የገለፁት ኮሙሽነሩ በዛሬው ዕለት የተካሄደው የ5 መቶ 50 ማህበራት የቦታ ርክክብ ስነ-ስርዓት የሚያሳየው ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ ትዕዛዙ በፀሃ ደግሞ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና ከንቲባ ኮሜቴ እንዲሁም ለተግባሩ ስኬት አስተዋፅዎ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃ ጽ/ቤትአቶ ሲሳይ አዳነ ደግሞ መንግስታችን ሰው ተኮር መሆኑን ያሳየበት ተግባር ነው ያሉት ኃላፊው የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በቅንነት ውሳኔ ለወሰኑ የከተማዋ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህ ዓመት ደግሞ በመመሪያው መሰረት ከ2009 ዓም ጀምሮ ተደራጅተው ወረፋቸውን በመጠባበቅ ላይ ለነበሩ ማህበራት ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግሩን በመረዳት መፍትሄ በመስጠት ላይ ሲሆን በ2018 ዓም ከዛሬ 6 ወር በፊት በድምሩ ለ69 ማህበራት ቦታ ተጠንቶላቸው የካሳ ክፍያ በመክፈል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ወረፋቸውን በመጠባበቅ ላይ ለነበሩ 550 የመኖሪያ ቤት ማህራት በዛሬው ዕለት የሳይትና የብሎክ ርክክብ ተደርጓል ብለዋል።
በአንድ ዓመት ብቻ በድምሩ 719 የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህራት ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ኃላፊው በበጀት ዓመቱ 15ሺ 818 ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው ተዋጽኦውን የጠበቀ ሴቶችን፣አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችን፣ የሀገር ባለውለታ የሆኑትን ምልስ ወታደሮችን፤ በስራ ላይ ያሉ የመከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ አካላትን፣የመንግስት እና የግል ትምህር ቤቶች መምህራንን ፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን እና ሰራተኞችን፣ የሆስፒታል እና የጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያዎችን፣ ከአረብ ሀገር ስደት ተመላሾችን፣ የሃይማት አባቶችን፣ በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞችን ፣ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን የተካተቱ መሆኑን አብራርተዋል።
ከ550 ማህበራት መካከል ለ26 ማህበራት በጎንደር ከተማ አስተዳደር ለሚሰሩ በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች ለሚሰሩ መምህራን ለዩኒቨርስቲ መምህራን 40 ማህበራት ለሆስፒታል እና ለሌሎች ጤና ባለሙያዎች14 ማህበራት በስራ ላይ ላሉ የመከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት 52 ማህበራት ለምልስ ወታደሮች 64 ማህበራት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በከተማችን ላሉ በርካታ ወጣቶች፣ ለመንግስት ሰራተኞች፣ ከአረብ አገር ስደት ተመላሾች፣ ለአካል ጉዳተኞች ለአይነ ስውራን እና ለሀይማኖት አባቶች 418 ማህበራት ናቸው፡፡
ማህበራት የተደራጁበትን ቀንና ዓ.ም ለመለየት የመስራች ቃለ ጉባኤያቸውን እና ሲደራጁ የከፈቱትን የባንክ አካውን ትና የተከፈተበትን ቀን መነሻ በማድረግ በቅደም ተከተል መሰጠቱን ተናግረዋል።
ቀሪ ማህበራት 597 በላይ አሉን ያሉት ጽ/ቤት ኃላፊው ከተማ አስተዳደሩ በከተማችን ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

